Federal Judicial Administration Council Secretariat

ክቡር አቶ ቡላ ዋጋሪ ቦርቶላ

የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጽ/ቤት ኃላፊ

የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጽ/ቤት ኃላፊ መልእክት

የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጽ/ቤት ቀደም ሲል በአዋጅ ቁጥር 684/2002 የተቋቋመ ሲሆን ከዚያም በፌደራል ዳኝነት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1233/2013 ሰፊ ሃላፊነት እና ተግባራት እንዲኖሩት ተደርጎ ተቋቁሟል፡፡የጉባኤ ጽ/ቤቱ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት እዉቅና የተሰጠዉን ተቋማዊ እና ግለሰባዊ የዳኝነት ነጻነትን፤ገለልተኝነት እና ተጠያቂነት የማረጋገጥ ኃላፊነት የተጣለበት ሲሆን ይህንንም የሚያሳካዉ በአዋጅ ቁጥር 1233/2013 የተሰጠዉን ሃላፊነት በመወጣት እና የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የሚያወጣቸዉን ህጎች፤መመሪያዎች እንዲሁም ዉሳኔዎችን በማስፈጸም እና በመከታተል ነዉ፡፡

የጉባኤ ጽ/ቤቱ በፌደራል ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች ላይ የሚቀርቡ የዲስፕሊን ክሶችን የመቀበል፤የቀረቡትን ክሶች በማደራጀት ለፌደራል ዳኞች ስነ ምግባር ኮሚቴ የመምራት፤በዳኞች ስነ ምግባር ኮሚቴ የዉሳኔ ሃሳብ የቀረበባቸዉን የዲስፕሊን ጉዳዮች ለፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የማቅረብ እና የዲስፕሊን ክሶችን በተመለከተ በጉባኤዉ የተሰጡ ዉሳኔዎችን የማስፈጸም እና አፈጻጸማቸዉን መከታተል ነዉ፡፡በዚሁ መሰረትም በዳኞች እና ሌሎች የጉባኤ ተሿሚዎች ላይ የሚቀርቡ የዲስፕሊን ክሶች በመቀበል፤መዝገብ በማደራጀት በጉባኤዉ ለተቋቋሙ የዳኞች ስነ ምግባር ኮሚቴዎች የማቅረብ ስራዎችን፤በጉባኤዉ ዉሳኔ የተሰጠባቸዉን የዲስፕሊን ክሶችም የማስፈጸም እና የመከታተል ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይ ጊዜያትም የዲስፕሊን ክሶቹ በተሻለ ፍጥነት ሊታዩ የሚችሉበትን ሁኔታ የማመቻቸት ስራዎችን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ወደፊት በዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች ላይ ዲፕሊን ክሶች እና ጥቆማዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ አቤቱታ አቅራቢዎች ካሉበት ቦታ ሆነዉ የሚያቀርቡበት ስርዓትን ለመዘርጋት ይሰራል፡፡

የጉባኤ ጽ/ቤቱ የዳኝነት ስራዉ በላቀ ጥራት እና ስነ ምግባር እንዲከናወን ለማስቻል የፌደራል ዳኞችን በተመረጡ ዘርፎች ስልጠና እንዲያገኙ የስልጠና እቅድ በማዉጣት፤ስልጠና እንዲያገኙ እና አቅማቸዉን እንዲያዳብሩ የማድረግ ኃላፊነት ያለበት ሲሆን ከዚህ ቀደም ሲሰጥ የነበረዉን ስልጠና ወደፊትም አጠናክሮ የመቀጠል ዓላማ በመያዝ እየተሰራ ይገኛል፡፡

በአጠቃላይ የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጽ/ቤት የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ እቅድ የማቀድ፤አፈጻጸሙን በተመለከተ ሪፖርት የማዘጋጀት፤እንዲሁም ጉባኤዉ በህግ የተጣለበትን ሃላፊነት እንዲወጣ አስፈላጊ የሆኑ ተግባራትን የሚሰራ ሲሆን ይህን ወደፊትም በመቀጠል የዳኝነት ስርዓቱ ነጻ፤ገለልተኛ እና ተጠያቂነት የተረጋገጠበት እንዲሆን የሚያስችሉ ተግባራትን ተጠናክረዉ የሚቀጥሉ መሆኑን ለማሳወቅ እወዳለሁ፡፡