Federal Judicial Administration Council Secretariat

የጽ/ቤቱ አመሰራረት

የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የአደረጃጀት ታሪክ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ከወጣው የአዋጅ ቁጥር 323/1965 ይጀምራል፡፡   በዚህ አዋጅ  ዳኞችን የመምረጥ ፤የዳኞችን የዓመት ፈቃድ ዳኞችን  የማዘዋወር፣የዳኞችን ደረጃ የማውጣት፤ የዳኞች ዲሲፕሊን እና የአፈጻጸም ጉድለቶች  ላይ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን በግልጽ ተለይቶ ለዳኞች አስተዳደር ጉባዔ  የተሰጠ ሲሆን አባላቱ የነበሩት የፍርድ ሚኒስቴሩ፤አፈንጉሱ፤የመንግስት ሰራተኞች ማስተዳደሪያና የጡረታ  ጉባዔ የበላይ ኮሚሽነር፤ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፤ጠቅላይ ዓ/ህግ ና በንጉሱ የሚሾሙ ሁለት  ሰዎችን በአባልነት ያቀፈ ሆኖ ጸሀፊው ከፍርድ ሚኒስቴር እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡  በአጠቃላይ አዋጁ ዳኞች ስራቸውን  በሙሉ ነጻነት እንደሚያከናውኑ ቢገልጽም ከአባላት ስብጥር እና ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮችን ለአስፈጻሚው እና ለንጉሠ ነገሥቱ አሳልፎ የሚሰጥ የነበረ  በመሆኑ ጉባዔው የታለመለትን  ዓላማ ሊያሳካ አልቻለም፡፡

በዘመነ ደርግ  አዋጅ ቁጥር  53/1968  መሰረት የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ እንደገና የተዋቀረ ሲሆን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፤የፍርድ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ፤የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፤ጠቅላይ አቃቤ ህግ፤ የመንግስት ሰራተኞች ማስተዳደሪያ ጠቅላይ መስሪያ ቤት የበላይ ኮሚሽነር እንዲሁም  በርዕሰ ብሄሩ የሚሾሙ ሶስት አባላት ያቀፈ ሲሆን ፀሃፊው  ከፍትህ ሚኒስቴር  ሹማምንት አንደሚመደብ ተገልጾል፡፡  ይህ አዋጅ አንደቀድሞ አዋጅ ዳኞች ስራቸውን በነጻነት እንደሚያከናውኑ ቢደነግግም የጉባዔው አደረጃጀት በንጉሱ ዘመን ከነበረው በላይ ለአስፈጻሚው አካል ትኩረት የሚሰጥ እና ርዕሰ ብሄሩን በንጉሱ ከመተካት ውጪ የተለየ ውጤት አላመጣም።

የፌደራሉ መንግስት ከመመስረቱ በፊት የመጨረሻው የዳኞች አስተዳደር ጉባኤአንደገና የተቋቋመው በሽግግሩ  ወቅት የፍትህ አስተዳደርን ከማንኛውም ተጽዕኖ ነጻ ለማድረግ በወጣው  አዋጅ ቁጥር 23/1984 አንቀጽ 8/1 መሰረት  ሲሆን የህገ መንግስቱን መውጣት ተከትሎም የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ  የተባለ ተቋም በአዋጅ ቁጥር 24/1988  ተቋቋመ፡፡  የጉባዔው አባላትም  በሶስቱም የፌደራል ፍርድ ቤት ደረጃ የሚገኙ ፕሬዝዳንቶች ፤የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት፤ ከፌደራል ጠቅላይ እና ከፍተኛ ፍርድ ቤት በስራ ቀደምትነት ያላቸውን አንድ አንድ ዳኞች እንዲሁም ሶስት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በአጠቃላይ ዘጠኝ አባለትን ያቀፈ ነበር፡፡ በዚህ አዋጅ ዳኞችን ለመመልመል ዝርዝር መስፈረቶች ቢቀመጡም የጉባዔው ጽ/ቤትን በተመለከተ ግን ምንም የተባለ ነገር አልነበረም፡፡  በመቀጠል በአዋጅ 24/1988 ላይ የነበሩትን ክፍተቶች ለመፍታት አዋጅ 684/2002 እንዲወጣ በማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ የጉባዔውን ቀን ተቀን  ስራዎች የሚሰራ  የራሱ ጽ/ቤት እንዲኖረው ተደረገ፡፡ ሆኖም ይህ አዋጅ  የዳኞች ነፃነት ከየትኛውም መንግሥታዊ  ሆነ ሌላ አካል  ነጻ ለማድረግ በህገመንግሰቱ  የተደነገገውን  ድንጋጌ በተሟላ መለኩ ለመፈጸም አላስቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት አሁን በስራ ላይ የሚገኘውን አዋጅ 1233/2013 በማውጣት የዳኞች ምልመላ ፤ ጥቅማጥቅም፤ስልጠና፤  የስራአፈጸጻም ምዘና ፤ሰነምግባር እና ዲስፕሊን  እና ሌሎች አስተዳደራዊ ስራዎች ትኩረት ተሰጥቶቸው እንዲሰሩ በማድረግ  በዳኝነት ዘርፉ ላይ ተገልጋዮች  እርካታ እና አመኔታ እንዲያሳድሩ  ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡